የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ) ከ190 በላይ የሆኑ አባል ድርጅቶችን ያቀፈ ለትርፍ ያልተቋቋመ እና መንግስታዊ ያልሆነ የሲቪል ማኅበራት ድርጅት ነው። ኅብረቱ በ2011 ዓ.ም. በፌዴራል ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ባለስልጣን (ACSO) በሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች አዋጅ ቁጥር 1113/2019 መሠረት በምዝገባ ቁጥር 4748 ፈቃድ አግኝቷል። ድርጅቱ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች በምርጫ ታዛቢነት፣ በሲቪክና መራጭ ትምህርት፣ በምርጫ ግጭቶች መከላከል እና ለአባላቱ አቅም ግንባታ ያላቸውን ሚና ለማሳደግና ለማስተባበር ነው።

ኅብረቱ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በ2011 ዓ.ም የሲዳማ ክልል ህዝበ ውሳኔ፣ በ2013 ዓ.ም አጠቃላይ ምርጫዎች (ሰኔ 21፣ 2013 ዓ.ም እና መስከረም 30 ቀን 2014)፣ በ2013 ዓ.ም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ህዝበ ውሳኔ፣ በ2015 ዓ.ም የደቡብ ኢትዮጵያ እና ወላይታ ዞን ድጋሚ ህዝበ ውሳኔ፣ እና በ2016 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አፋር፣ መካከለኛው ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ክልሎች አንዳንድ ክፍሎች የተካሄዱትን ቀሪ እና ድጋሚ ምርጫዎችን ታዝቧል። በተጨማሪም ኅብረት ለምርጫ የተለያዩ የአድቮኬሲ እና የስነ_ዜጋ ትምህርት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ዴሞክራሲያዊ ተቋማትን እና የዜጎችን ተሳትፎ ለማጠናከር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን አድርጓል።

ኅበረቱ ለሚመጣው 7ኛው ጠቃላላ ምርጫ የምርጫ ትዝብት ላይ የባለሙያ ምክር ለማግኘት የቴክኒክ አማካሪ ኮሚቴ የማቋቋም ሂደት ላይ ይገኛል። ይህ አማካሪ ኮሚቴ ለኅብረቱ ቦርድ ትክክለኛ፣ ገለልተኛ እና ሞያዊ ብቃት ያለውን የምርጫ ትዝብት ለማረጋገጥ ከፍተኛ ደረጃ ያለው የቴክኒክ ምክር፣ ትንተና እና የአደጋ ግምገማ በማቅረብ ቋሚ የባለሙያዎች ኮሚቴ ሆኖ ያገለግላል። ኮሚቴው በጋና እና ኬንያ ከሚገኙ የኅብረት ለምርጫ አቻ የዜጎች ታዛቢ ቡድኖች ካላቸው ተመሳሳይ ተሞክሮ በመነሳሳት ሪፖርቶችን በመገምገም፣ በህግ እና በደህንነት አደጋዎች ላይ በማማከር እና የምርጫ ክስተቶችን በመተንተን የኅብረቱን የምርጫ ትዝብት ታዓማኒ እንዲሆኑ ያደርጋል።

ኅብረት ለምርጫ ለዚህ ኮሚቴ አባልነት ብቁ የሆኑ ግለሰቦችን (ራስን ጨምሮ) ለመመልመል ሁሉም ዜጎች፣ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች፣ የትምህርት ተቋማት እና የሙያ መረቦች ጥሪ ያቀርባል። ይህ ህዝባዊ ጥሪ የባለሙያነት፣ የቅንነት እና የኢትዮጵያን ብዝሃነት የሚያንፀባርቅ ውክልናን ቅድሚያ የሚሰጥ የተለያየ እና በብቃት ላይ የተመሠረተ የምርጫ ሂደት ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

የአማካሪ ኮሚቴው ስብጥር

ኮሚቴው ስድስት (6) አባላት የሚኖሩት ሲሆን፣ ከሚከተሉት ዘርፎች አንድ ባለሙያ ይመረጣል፡

  1. ህግ (የምርጫ ህግ፣ የህገ መንግስት ህግ፣ ወይም የሰብዓዊ መብት)
  2. ፖለቲካል ሳይንስ (የፖለቲካ፣ የግጭት እና የምርጫ ሂደቶች ትንተና)
  3. ስታቲስቲክስ (ስታቲስቲክስ፣ የዳታ ትንተና)
  4. የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ (ዲጂታል ደህንነት፣ የምርጫ ቴክኖሎጂ፣ ወይም የዳታ ሲስተሞች)
  5. ጋዜጠኝነት እና ኮሙዩኒኬሽን (ስትራቴጂክ ኮሙዩኒኬሽን)
  6. የደህንነት አደጋ ግምገማ (የግጭት ትንተና ወይም የደህንነት መመሪያዎች)

የአባልነት መስፈርቶች

እጩዎች የሚከተሉትን ዝቅተኛ መስፈርቶች ማሟላት አለባቸው፡-

  • በተጠቀሱት መስኮች በአንዱ የትምህርት ዲግሪ ሊኖራቸው ይገባል።
  • በሙያ ዘርፋቸው ቢያንስ አምስት (5) ዓመታት የሥራ ልምድ ሊኖራቸው ይገባል።
  • ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች፣ ገለልተኝነት እና ወገንተኝነት የሌለው አቋም ማሳየት (በምርጫ ሂደት ውስጥ ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እጩዎች ጋር ግንኙነት የሌለው)።
  • ጠንካራ የሥነ ምግባር ደረጃዎች፣ ከገለልተኝነት እና ታማኝነት ጋር የተያያዘ ባህሪ ያለው።

የኢትዮጵያን ብዝሃነትን ለማንፀባረቅ በፆታ፣ የአካል ጉዳት፣ የብሄር ለማካተት ጥረት ይደረጋል። አባላት ለሁለት ዓመት የአገልግሎት ዘመን ያለምንም ክፍያ በበጎ ፈቃድ ያገለግላሉ።

እጩ እንዴት ማቅረብ ይቻላል?

እጩ አባል ለመጠቆም (ወይም ራስን ለመጠቆም) የሚከተሉትን ሰነዶች ማስገባት ያስፈልጋል፡-

  • እራሳቸውን ለሚጠቁሙ አመልካቾች ብቃታቸውን ፣ ልምድ እና ተዛማጅ ስኬቶችን የሚያሳይ የሥራ ልምድ (CV)።
  • ተነሳሽነት፣ ሙያዊ እውቀታቸው ከኅብረት ለምርጫ ተልዕኮ ጋር እንዴት እንደሚጣጣም፣ እና ለዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደቶች ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያብራራ የፍላጎት መግለጫ (1 ገጽ)
  • ሌላ ሰው የሚጠቁሙ ከሆነ፣ እጩዎቹን የተመለከተ አስፈጊ መረጃዎችን ፤ እንዲሁም መስፈርቶቹን የሚያሟሉ እንደሆኑ ለምን እንደሚያምኑ የሚያብራራ አጭር መግለጫ ማካተት

ማመልከቻዎች በኢሜል ወደ info@cecoe.org (ወይም በድረ-ገጻችን ማስገቢያ ቅጽ ወይም www.cecoe.org) መላክ አለባቸው።

ጠቋሚዎች በሚጠቁሙበት በኢሜሉ ርዕስ ላይ “ለአማካሪ ኮሚቴ እጩነት” በማለት የተወሰነውን መስክ ማመልከት አለባቸው።

ማመልከቻዎችን ለማስገባት የመጨረሻ ቀን : የካቲት 28 ቀን 2028 ዓ.ም.

ዘግይተው የሚቀርቡ ማመልከቻዎች ተቀባይነት አይኖራቸውም።

የምርጫ ሂደት

ሁሉም እጩዎች ግልጽ በሆነ እና በብቃት ላይ በተመሠረተ ግምገማ ውስጥ ያልፋሉ፡-

  1. ዝቅተኛው መስፈርት መሟላቱን ለማረጋገጥ በኅብረት ለምርጫ  ሴክሬታሪያት የመጀመሪያ ደረጃ ማጣሪያ።
  2. ቃለ-መጠይቆችን ወይም የማጣሪያ ጥሪዎችን ሊያካትት በሚችል የማጣሪያ ንዑስ ኮሚቴ ግምገማ።
  3. የመጨረሻ ምክረ ሃሳብ ለኅብረት ለምርጫ ቦርድ ቀርቦ ይጸድቃል። 

የተመረጡት አባላት እስከ መጋቢት 31 ቀን 2026 ዓ.ም. ይነገራቸዋል።

ለምን ይሳተፋሉ?

ባለሙያዎችን በመጠቆም የኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሂደቶች ለማጠናከር ይረዳሉ። አማካሪ ኮሚቴው ለ7ኛው አጠቃላይ ምርጫ ታማኝነት አስተዋፅዖ በማድረግ፣ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚጠቅም ወቅታዊ እና ሙያዊ ምልከታን በማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

ለጥያቄዎች ወይም ለተጨማሪ መረጃ፣ የእኛን ሴክሬታሪያት በ info@cecoe.org ያግኙ።

የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ)

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ