የኅብረት ለምርጫ ምልከታ በ6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ የምርጫ ቦርድ የምርጫ ሰራተኞች ምልመላ እና ስልጠና ጥራት
በኢትዮጵያ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም እና መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደ ሲሆን፤ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና በክልል ምክር ቤቶች ለአምስት ዓመታት የሚያገለግሉ የህዝብ ተወካዮች ተመርጠዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ እንዲያዘጋጅ ህጋዊ ስልጣን የተሰጠው ሲሆን፤ በምርጫ ሕጉ መሰረት ከምርጫ ቦርድ ስልጣን አንዱ የምርጫ ክልሎችን፣ የምርጫ ጣቢያዎችን እና የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶችን ማቋቋም ነው። በዚህም መሰረት ለጠቅላላ የምርጫ ዑደት አስተማማኝነት ወሳኝ የሆኑ የመራጮች ምዝገባ፣ የዕጩዎች ምዝገባ፣ የድምጽ መስጫ ቀን አፈፃፀም እንዲሁም የድህረ- ምርጫ ሂደቶችን ያካተቱ የምርጫ ተግባራት የሚከናወኑት በእነዚሁ በሕግ በተቋቋሙ መዋቅሮች ነው። እነዚህ መዋቅሮች በመራጮች ምዝገባ፣ በእጩዎች ምዝገባ እና በድምጽ መስጫ ቀን አብዛኛውን የምርጫ ተግባራትን የማከናወን ኃላፊነት በተሰጣቸው የምርጫ አስፈፃሚዎች የተመሰረቱ ናቸው።
በኢትዮጵያ ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫን የማዘጋጀት ህጋዊ ግዴታውን ለመወጣት የምርጫ ቦርድ በምርጫ ጣቢያ፣ በምርጫ ክልል እና በክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ደረጃ ከ150,000 በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎችን መልምሎ፣ በማሰልጠን፣ አሰማርቷል። ኅብረት ለምርጫ በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ባደረገው ትዝብት እነዚህ የምርጫ አስፈፃሚዎች የምርጫ ሕጉ በሚያስቀምጠው መሰረት ምርጫን ለማስፈፀም የሚጠይቃቸው የቴክኒክ እና የስነምግባር አቅም ክፍተቶች እንደነበሩ ለማረጋገጥ ተችሏል። በአንዳንድ የምርጫ አስፈጻሚዎች የቴክኒክ እና የስነምግባር አቅም ማነስ ምክንያት ምርጫ ቦርድ በአንዳንድ ምርጫ ጣቢያዎች እና ምርጫ ክልሎች ውጤቱን ለመሰረዝ ተገዷል