ከምርጫ ጋር በተገናኘ የሚነሱ ቅሬታዎችን በወቅቱ እና በአግባቡ ለመፍታት የምርጫ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችን (Grievance Hearing Committees) በተፈላጊው መጠን መመስረት እና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ ወሳኝ ነው። የእነዚህን ኮሚቴዎች ውጤታማነት እና ቅልጥፍና ማረጋገጥ የተግባራዊነት መስፈርቶችን ከአቤቱታ አቅራቢዎች መብት ጋር የሚያመዛዝን ተግባራዊ የህግ ማዕቀፍ ማውጣትን ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ምርጫ አዋጅ እና ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች ማቋቋሚያ እና አሰራር መመሪያ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በምርጫ ጣቢያ፣ በምርጫ ክልል እና በክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ደረጃ ባሉ የምርጫ አፈጻጸም መዋቅሮች ላይ ሶስት ሶስት አባላት ያሏቸው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎችን ያቋቋማሉ።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ቦርዱ) በህግ የተቋቋሙትን ኮሚቴዎች በአግባቡ መጠቀም አለመቻሉን የኅብረት ለምርጫ የስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ትዝብት ሪፖርት ያሳያል። በዚህም የተነሳ ቅሬታ አቅራቢዎች (መራጮች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ሌሎች) ከሕግ ውጪ ለሆኑ አሰራሮች እንደተጋለጡ የኅብረት ለምርጫ ትዝብት ያመለክታል። በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጾችን ከማጣራት እና ከመቁጠር ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮችን ፣የፓርቲ ተወካዮችን ከምርጫ ቆጠራ ሂደት ማባረር፣ መራጮችን ማስፈራራት፣ የገዥው ፓርቲ አባላት ጣልቃ ገብነት፣ በተንቀሳቃሽ የምርጫ ታዛቢነት እንዳይሳተፉ በባለሥልጣናት/ በአስተዳዳሪዎች መገደብ የመሳሰሉት ቅሬታዎች ቀርበው ነበር።

ይህ የፖሊሲ ፍሬ ሃሳብ በፖሊሲ አውጪዎች በተለይም ቦርዱ በኢትዮጵያ የምርጫ ቅሬታ አሰማም ዘዴ ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ አሳማኝ ሃሳብ ለማቅረብ ያለመ ነው። በዚህ ሰነድ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የተለያዩ ምክረ-ሃሳቦች ተሰጥተዋል። በዚህም መሰረት ቦርዱ አሁን በሕግ የተደነገገው የምርጫ ቅሬታ አሰማም ሂደት ካሉበት ተግባራዊ ውሱንነት አንፃር በማሻሻል የቅሬታ አሰማም ሂደቶች ተግባራዊ መሆናቸውን ሊያረጋግጥ ይገባል። ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅሬታቸውን በሚያቀርቡበት ጊዜ ሁሉንም የሕግ እና የተቋም መስፈርቶች የሚከተሉ እንዲሆኑ አቅማቸውን ማሳደግ። በተጨማሪም የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች አባላትን በመመልመል እና በማሰልጠን ለምርጫ ቦርድ ድጋፍ ማድረግ አለባቸው። ከዚህም ባለፈ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የኢትዮጵያ የምርጫ ቅሬታ አሰማም ዘዴ ሕግን የሚመለከቱ ስልጠናዎችን ለፖለቲካ ፓርቲዎች መስጠት አለባቸው።

FileAction
Electoral Grievance Hearing Mechanism in Ethiopia Amharic.pdfDownload