ሰኔ 15፣ 2016 ዓ.ም
ኅብረት ለምርጫ
አዲስ አበባ
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ደረጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአፋር፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና ሶማሌ ክልሎች የሚካሄደውን ቀሪ እና የድጋሚ ምርጫ ለመታዘብ ዝግጅቱን አጠናቅቋል።
ቀደም ሲል ኅብረት ለምርጫ የቅድመ ምርጫ ከባቢን ለመታዘብ በአሶሳ፣ ሰመራ፣ ቡታጅራ እና ጅግጅጋ ከሚንቀሳቀሱ አባል ድርጅቶቹ የተውጣጡ 15 የረጅም ጊዜ ታዛቢዎችን በመመልመል የአንድ ቀን ስልጠና ሰጥቶ ማስማራቱ ይታውቃል።
በተመሳሳይም ኅብረት ለምርጫ በድምጽ መስጫ ቀን የድምጽ አስጣጥ ሂደቱን የሚታዘቡ የአጭር ግዜ ታዛቢዎች አስፈላጊው ክህሎትና እውቀት እንዲኖራቸው ሰኔ 12 እና 13 ቀን 2016 ዓ.ም በአሶሳ፣ ሰመራ፣ ቡታጅራ እና ጅግጅጋ ከተሞች 84 ታዛቢዎች የአንድ ቀን ስልጠናዎችን ሰጥቷል። ከዚህ በተጨማሪም ለአጭር ግዜ ታዛቢወች የጽሁፍ መልዕክትን እና የአፖሎ ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትዝብት ሪፖርታቸውን ወዲያውኑ በኅብረት ለምርጫ ፅ/ቤት ውስጥ ለተቋቋመው የመረጃ ማዕከል ሪፖርት ማድረግ የሚያስችላቸወን በተግባር የተደገፈ ስልጠና ከመስጠቱም በላይ የማስመሰል(ሲሚዩሌሽን) ልምምዶችን አዘጋጅቶላቸዋል።
ኅብረት ለምርጫ ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ በአጠቃላይ 84 ተቀማጭ ታዛቢዎችን ለማስማራት አቅዷል። እነዚህ ተቀማጭ የድምጽ መስጫ ቀን ታዛቢዎች በየተመደቡባቸው የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ቀኑን ሙሉ የምርጫውን ሂደት እየታዘቡ የሚቆዩ ይሆናል።
በመጨረሻም ኅብረት ለምርጫ የቅድመ-ምርጫ፣ የድምጽ መስጫ ቀን እና የድህረ-ምርጫ የትዝብት ግኝቶችን ያካተተ አጠቃላይ ሪፖርት ይፋ የሚያደርግ መሆኑን መግለጽ ይወዳል።