በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ10 የሚበልጡ ዞኖች ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የራሳቸውን ክልላዊ መንግሥት ለመመስረት ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወቃል። በዚህም መሰረት በሕዳር 2011 ዓ.ም እና በመስከረም 2014 ዓ.ም ከተካሄዱ የሕዝበ ውሳኔዎች በኋላ የሲዳማ ክልል እና የደቡብ ምዕራብ ክልሎች ተመስርተዋል።

በተመሳሳይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች አዲስ ክልል እንዲመሰረት በየምክር ቤቶቻቸው አማካኝነት ውሳኔ አሳልፈዋል። በዚህም መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስማቸው ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሕዝበ-ውሳኔ እንዲያደራጅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያ ሰጥቷል። የምርጫ ቦርድም ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በስድስቱ ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ እና ጎፋ) እና በደቡብ ክልል አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ እና ደራሼ) ሕዝበ ውሳኔ ማካሄዱ ይታወሳል። ኅብረት ለምርጫም በስድስቱ ዞኖችና በአምስቱ ልዩ ወረዳዎች 434 ተቀማጭ እና 76 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን መልምሎ በማሰልጠን ለትዝብት አሰማርቷል። ነገርግን የምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ እና በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ከፍተኛ የሆነ የህግ ጥሰት መፈፀሙን በመጥቀስ በወላይታ ዞን የተካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ሰርዟል። ይህንንም ተከትሎ የምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝበ ውሳኔው በድጋሚ እንደሚካሄድ ለባለድርሻ አካላት አስታውቋል። በዚህም መሰረት ኅብረት ለምርጫ ለወላይታ ዞን አዋሳኝ በሆኑ ዞኖች የሚገኙ ስድስት አባል ድርጅቶቹን በማሳተፍ 190 ታዛቢዎችን መልምሎ፤ ከመካከላቸው በአጠቃላይ 146 (118 ተቀማጭ እና 28 ተንቀሳቃሽ) ታዛቢዎችን አሰማርቶ የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን በመታዘብ  ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርት አዘጋጅቷል። 

FileAction
Preliminary Report by CECOE - Referendum rerun in the Wolaita zone.pdfDownload