መግቢያ

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ) በ2011 የተቋቋመ ሲሆን የሲቪል ማህበራት በምርጫ ትዝብት ፣ ክትትል፣  የመራጮች ትምህርት እና ከምርጫ በኋላ ግጭቶችን በመከላከል ላይ ያላቸውን ሚና ለማሳደግ እና ለማስተባበር የተቋቋመ ነው። ኅብረት ለምርጫ በተመሰረተ ማግስት የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን በተቀናጀ መልኩ በመታዘብ በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ውስጥ አዲስ ምዕራፍን ከፍቷል። ይህንን ልምድ በመቀመር በስድስተኛው የኢትዮጵያ ብሔራዊ እና ክልላዊ ምርጫ ኅብረት ለምርጫ ከ3,500 በላይ የረጅም ጊዜ እና የአጭር ጊዜ ታዛቢዎችን በዘጠኝ ክልሎች እና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች መልምሎ በማሰልጠን አሰማርቷል። ይህም ሰኔ 2013 ዓ.ም እና መስከረም 2014 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ እና በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ የተካሄዱትን ምርጫዎች ያካትታል። በመቀጠልም በጥር ወር 2015 ዓ.ም በደቡብ ክልል ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች የተካሄደውን ህዝበ ውሳኔ እና በሰኔ 19 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደውን የወላይታ ዞን ድጋሚ ህዝበ ውሳኔ በተሳካ ሁኔታ ታዝቧል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን እና አዲስ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሹመትን ወሳኝነት በመገንዘብ ኅብረቱ የምርጫ ቦርድን ሰብሳቢ የአመላመል እና ሹመት ሂደት በቅርበት ተከታትሏል።  ይህ የግምገማ ሪፖርት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢን ምልመላ፣ አመራረጥ እና የሹመት ሂደት እንዲሁም ሂደቱ ሕጉን የተከተለ ስለመሆኑ በሚዲያ የወጡ ሪፖርቶች እና መልማይ ኮሚቴው በሰጣቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ላይ በመመስረት በዝርዝር ፈትሿል። ሪፖርቱ እንደ ግልፅነት፣ አካታችነት እና አሳታፊነት ያሉ ዋና ዋና የፖለቲካ ሂደትን መመዘኛዎችን በመጠቀም ለወደፊት ለሚከናወኑ የአሿሿም ሂደት ለማሻሻል ምክረ-ሃሳቦች ለመስጠት ሞክሯል። ይህም የዲሞክራሲያዊ መርሆዎችን ለማስከበር፣ ዜጎች በምርጫ ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲያድርባቸው፣ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ አመራረጥን በተመለከተ ግልጽና በበቂ መረጃ ላይ የተመሰረተ ውይይት ለማድረግ የበኩሉን አስተዋጽዖ በማበርከት፣ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ምርጫዎች ተዓማኒነት እና ቅቡልነት ለማረጋገጥ ቁልፍ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።

FileAction
nebe amharic.pdfDownload