በኢፌዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 47 (2) በአንቀጽ 47 (1) በተዘረዘሩት ክልሎች ውስጥ የተካተቱት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን ክልል የመመሥረት መብት ክልል የመመሥረት ጥያቄው በብሔሩ፣ በብሔረሰቡ ወይም በሕዝቡ ምክር ቤት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ማግኘቱ ሲረጋገጥ እና ጥያቄው በጽሑፍ ለክልሉ ምክር ቤት ሲቀርብ፣ ጥያቄው የቀረበለት የክልል ምክር ቤትም ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለጠየቀው ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሕዝበ ውሳኔ ሲያደራጅ፣ ክልል የመመሥረት ጥያቄው ሕዝበ ውሳኔውን ባካሄደው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ በአብላጫ ድምፅ ድጋፍ ሲያገኝ፣ እና የክልሉ ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄ ላቀረበው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሥልጣን ሲያስረክብ ከላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች ከተሟሉ በሕዝበ ውሳኔው የሚፈጠረው አዲስ ክልል ጥያቄ ማቅረብ ሳያስፈልገው በቀጥታ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ አባል እንደሚሆን ሕገ መንግሥቱ ይደነግጋል።

ባለፉት አራት አመታት ውስጥ የደቡብ ክልል ሶስት የክልልነት ህዝበ ውሳኔዎች የተካሄዱ ሲሆን ይህ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ያካሄዱት ሕዝበ- ውሳኔ ሶስተኛው ነው። የደቡብ ክልል በ2012 ዓ.ም የሲዳማ ሕዝበ-ውሳኔን፣ በ2014 ዓ.ም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሕዝበ-ውሳኔን ማስተናገዱ የሚታወስ ነው። የስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች የክልልነት ጥያቄ ለፌዴሬሽን ምክርቤት የቀረበው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝበ-ውሳኔ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ላይ የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎችን መፍትሄ እንዲያፈላጉ የተሾሙ የሰላም አምባሳደሮች1 ባደረጉት አነሳሽነት እና የስድስቱ ዞኖች እና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች ምክር ቤቶች ለፌደሬሽን ምክርቤት ባቀረቡት ማመልከቻ መሰረተ ነው። የፌደሬሽን ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ ተቀብሎ አጸድቆ ለኢትዬጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ-ውሳኔውን እንዲያስፈጽም ትዕዛዝ ማስተላለፉን ተከትሎ ሕዝበ- ውሳኔው ተግባራዊ ሆኗል።

ኅብረት ለምርጫም በደቡብ ክልል ለሶስተኛ ጊዜ የተካሄደውን የሕዝበ-ውሳኔ ወሳኝ ሂደቶችን ማለትም የቅድመ- ሕዝበ ውሳኔን፣ የሕዝበውሳኔ ምርጫ ቀንን እንዲሁም ድህረ-ሕዝበ ውሳኔን ታዝቧል። በተጨማሪም በወላይታ ዞን የተካሄደውን የደጋሚ ህዝበ ውሳኔ ሂደት ታዝቧል። በዚህም መሰረት ኅብረት ለምርጫ በትዝብት ሥራው የደረሰባቸውን አንኳር ግኝቶች በሚከተለው ክፍል ይዳስሳል።

FileAction
የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝበውሳኔ እና የወላይታ ዞን ድጋሚ ሕዝበ-ውሳኔ አጠቃላይ የትዝብት ሪፖርት.pdfDownload