Aug 2, 2023
ይህ የፖሊሲ ማብራሪያ በመገናኛ ብዙሃን እና በምርጫ መካከል ያለውን ግንኙነት አስፈላጊነት ከግምት ውስጥ በማስገባት በኢትዮጵያ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዙሪያ ያሉትን ተግዳሮቶች፣ አንድምታዎች እና ተስፋዎች እና የመገናኛ ብዙሃን የተለያዩ የምርጫ ባለድርሻ አካላትን ተደራሽነት ይዳስሳል። ከዚህ ባለፈም የሚዲያ ተቋማት የጋዜጠኝነት ሞያ ስነ-ምግባር አክብረው በምርጫው ሂደት ላይ ሚዛናዊ ሽፋን መስጠት እንዳለባቸው ያትታል። በተጨማሪም የመራጮች ትምህርት የሚዲያ ሽፋን ማሳደግ እና ሴቶችን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በምርጫ ወቅት በሚዲያ ሽፋን በበቂ ሁኔታ እንዲወከሉ የማድረግን አስፈላጊነት አጉልቶ ያሳያል።
በኅብረት ለምርጫ የሚዲያ ክትትል ክፍል ዘገባ ላይ በመመስረት፤ 6ተኛው ጠቅላላ ምርጫ በተካሄደበት ወቅት፣ ከምርጫ ጋር የተያያዙ ርዕሰ ጉዳዮች ብዙውን ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን ሽፋን ቢያገኙም፤ ነገር ግን የሚዲያ ሽፋን በሌሎች ከምርጫ ጋር ያልተገናኙ የፖለቲካ ጉዳዮች () አብላጫ የሆኖ ሽፋን አግኝተው ነበረ። በምርጫ ክርክሮች ላይ 12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሳተፉም በትላልቅ የክርክር መድረኮች 5 የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ነበር የተሳተፉት። የጋዜጠኝነት ሞያዊ ሥነ ምግባርን አክብሮ መዘገብ ላይ ከሚዲያ ሚዲያ ልዩነት ነበረ። ከዚህም ባለፈ አብዛኛው ሚዲያ የምርጫ ቅስቀሳን ሚዛናዊነት በጠበቀ መልኩ ከመገናኛ ብዙሀን ህጎች እና ከምርጫ ቦርድ መመሪያዎች ጋር በተስማማ ሁኔታ ማቅረብ አልቻሉም ነበር። ገዥው ብልፅግና ፓርቲ ከሌሎች የምርጫ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛውን ሽፋን ያገኘ ሲሆን በተጨማሪም ሚዲያዎች ከምርጫ ጋር በተገናኘ ለሴቶች የሰጡት ሽፋን በጣም አነስተኛ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ በምርጫ ወቅት ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ከቀደምት የስኬት ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ እና በመጪው ምርጫ የሚዲያው ዘርፍ የላቀ ሚና እንዲኖረው መሻሻል በሚገባቸው ዘርፎች ላይ አተኩሮ ሊሰራ ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ሚናው ተቆርጦ በቀደመው ምርጫ ወቅት እንደነበረው ይቆያል።
Jun 29, 2023
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ የሚገኙ ከ10 የሚበልጡ ዞኖች ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የራሳቸውን ክልላዊ መንግሥት ለመመስረት ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወቃል። በዚህም መሰረት በሕዳር 2011 ዓ.ም እና በመስከረም 2014 ዓ.ም ከተካሄዱ የሕዝበ ውሳኔዎች በኋላ የሲዳማ ክልል እና የደቡብ ምዕራብ ክልሎች ተመስርተዋል።
በተመሳሳይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ስር የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎች አዲስ ክልል እንዲመሰረት በየምክር ቤቶቻቸው አማካኝነት ውሳኔ አሳልፈዋል። በዚህም መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስማቸው ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ሕዝበ-ውሳኔ እንዲያደራጅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ መመሪያ ሰጥቷል። የምርጫ ቦርድም ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በስድስቱ ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ እና ጎፋ) እና በደቡብ ክልል አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ እና ደራሼ) ሕዝበ ውሳኔ ማካሄዱ ይታወሳል። ኅብረት ለምርጫም በስድስቱ ዞኖችና በአምስቱ ልዩ ወረዳዎች 434 ተቀማጭ እና 76 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን መልምሎ በማሰልጠን ለትዝብት አሰማርቷል። ነገርግን የምርጫ ቦርድ በመራጮች ምዝገባ እና በድምጽ አሰጣጥ ሂደት ከፍተኛ የሆነ የህግ ጥሰት መፈፀሙን በመጥቀስ በወላይታ ዞን የተካሄደውን ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ሰርዟል። ይህንንም ተከትሎ የምርጫ ቦርድ በወላይታ ዞን ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. የሕዝበ ውሳኔው በድጋሚ እንደሚካሄድ ለባለድርሻ አካላት አስታውቋል። በዚህም መሰረት ኅብረት ለምርጫ ለወላይታ ዞን አዋሳኝ በሆኑ ዞኖች የሚገኙ ስድስት አባል ድርጅቶቹን በማሳተፍ 190 ታዛቢዎችን መልምሎ፤ ከመካከላቸው በአጠቃላይ 146 (118 ተቀማጭ እና 28 ተንቀሳቃሽ) ታዛቢዎችን አሰማርቶ የመራጮች ምዝገባ እና የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱን በመታዘብ ይህንን የመጀመሪያ ደረጃ የትዝብት ሪፖርት አዘጋጅቷል።
Jun 4, 2023
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች (ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ) እና አምስት ልዩ ወረዳዎች (ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ) የሚካሄደውን ሕዝበ-ውሣኔ ለመታዘብ ህዝበ-ውሳኔ ከሚካሄድባቸው ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች 434 ተቀማጭ እኛ 76 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን አሰማርቷል።
Jun 4, 2023
በ2013 ዓ.ም የተካሄደው የኢትዮጵያ ስድስተኛው አገር አቀፍ እና የክልል ምክር ቤቶች ምርጫ በአገሪቱ ከ2010 ዓ.ም አንስቶ የሚታዩትን ዲሞክራሲያዊ ጅማሮዎች ለማስቀጠል ወሳኝ መሰረትን ጥሏል። በአዲስ መልክ የተቀረፀው የምርጫ ህግና የቁጥጥር ማዕቀፍ ምርጫው ይበልጥ ንቁ የፖለቲካ ፉክክር እንዲታይበት፣ የዳኝነት አካሉ በምርጫ ሂደቱ ወሳኝ ሚናን እንዲጫወት እና ፣ ለሲቪል ማህበረሰቡ ተሳትፎ ሰፋ ያለ ምህዳር እንዲኖር አስችሏል። በተጨማሪም በ2013 ዓ.ም የተከናወነው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ከ1997ቱ ምርጫ በኋላ የሲቪል ማኅበራት በምርጫ ታዛቢነት እንዲሳተፉ በማስቻል በምርጫ ሂደቱ ላይ ትርጉም ያላቸው ግምገማዎችን እንዲያደርጉ ያስቻለ ምርጫ ሆኖ አልፏል። ከእነዚህ ለውጦች ጋር በተያያዘ ምርጫው የኢትዮጵያ ዜጎችን ጨምሮ በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪል ማኅበራት እና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት ዘንድ ካለፉት ምርጫዎች ይልቅ የበለጠ አካታች፣ ተጠያቂነትና ግልጽነት የሰፈነበት ይሆናል ተብሎ እንዲጠበቅ አድርጐታል። ምንም እንኳን በቅድመ ምርጫ፣ የድምፅ መስጫ ቀንና በድኅረ ምርጫ ሂደቶች ወቅት በግልጽ ጉድለቶች ቢስተዋሉም፤ በምርጫው ሂደት ህብረቱ የታዘባቸው ትርጉም ያላቸው መሻሻሎች አገሪቱ በቀጣይ ለምታደርጋቸው ምርጫዎች መሠረት ጥሎ አልፏል።