የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ)

መግቢያ  

የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ)፣ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባገኘው የትዝብት ፈቃድ፣ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በመታዘብ ላይ ይገኛል። ኅብረቱ የመራጮች ምዝገባ ሂደትን የሚታዘቡ 522 የረዥም ጊዜ ታዛቢዎችን ከትግራይ ክልል እና አከራካሪ ከሆኑ ቦታዎች በስተቀር በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች እና የከተማ መስተዳደሮች አሰማርቶ ሲታዘብ ቆይቷል።

ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በማኑዋል(manual) እና በታብሌት በመታገዝ ያካሄደውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት ኅብረት ለምርጫ ስልታዊ (Systematic) በሆነ መንገድ ፤ ወጥነት ያላቸውን የትዝብት ቅጾች (Checklists) በመጠቀም በተመረጡ አመላካቾች (Key indicators) መዝኗል። ይህ ሪፖርት በዋነኝነት የመራጮች የምዝገባ ሂደት፤ የሂደቱን አካታችነት (ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና አቅመ ደካሞችን ማሳተፉ)፤ በምዝገባ ጣቢያዎች አካባቢ የነበረው የጸጥታ አስከባሪዎች ስምሪት እና የምርጫ ደህንነትን ዳስሷል። 

ሪፖርቱ ከመጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ምዝገባው እስከተጠናቀቀበት ሚያዚያ 14 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ያለውን የመራጮች ምዝገባ ሂደት የሚሸፍን ሲሆን ኅብረት ለምርጫ 522 የረዥም ጊዜ ታዛቢዎችን ባሰማራባቸው 3,953 የማኑዋል እና 443 የታብሌት በአጠቃላይ ከ4,396 የምዝገባ ጣቢያዎች በተሰበሰቡ ግኝቶች ላይ የተመሰረት ነው። 

በዚህ ሪፖርት የቀረቡት ማንኛውም በመቶኛ (%) የተቀመጡ ግኝቶች ኅብረቱ ከታዘባቸው 3,953 የማኑዋል እና 443 የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች አኳያ የተሰሉ ናቸው።

የምዘገባ ጣቢያዎች አደረጃጀት እና ተደራሽነት

  • የምዝገባ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ሥፍራን በተመለከተ ኅብረቱ በታዘባቸው 3,851 (97%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 429 (97%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች በህጉ በተፈቀዱ ቦታዎች ተቋቁመዋል። ይሁን እንጂ 102 (3%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 14 (3%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ክልከላ በተደረገባቸው ቦታዎች (ወታደራዊ፣ ፖሊስ፣ ሃይማኖታዊ፣ ጤና ጣቢያ፣ መጠጥ ቤት/ሆቴል፣ የፖለቲካ ፓርቲ ጽህፈት ቤት እና የግል መኖሪያ ቤት) ተቋቁመዋል። 
  • የምርጫ አስፈጻሚዎች መሟላትን በተመለከተ ህጉ በምዝገባ ጣቢያዎች ቢያንስ ሶስት (3) የምርጫ አስፈጻሚዎች መገኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል። የኅብረቱ ታዛቢዎች በታዘቧቸው በሁለቱም የምዝገባ አማራጮች ምዝገባ በተደረገባቸው ጣቢያዎች በአማካይ 4 አስፈፃሚዎች መኖራቸው ተረጋገጧል።
  • የምዝገባ ጣቢያዎች የተከፈቱበትን ሰዓት በተመለከተ በ1,284 (63%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና በ125 (56%) የታብሌት ጣቢያዎች የምዝገባውን ሂደት ከጠዋት ከ2፡30 እስከ 3፡30 ባለው ሰዓት አስጀምረዋል። በአንጻሩ በ762 (37%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና በ98 (44%) የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ምዝገባው ከ3፡30 እስከ እኩለ ቀን (6፡00 ሰዓት) ተጀምሯል። ትዝብት በተደረገባቸው 5 የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እስከ እኩለ ቀን (6፡00 ሰዓት) የምዝገባ ሂደቱ አልተጀመረም። 
  • የምርጫ አስፈጻሚዎች የምሳ ዕረፍት አጠቃቀምን በተመለከተ በከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ ትዝብት ከተደረገባቸው 1,902 የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 220 የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች መካከል በ1,702 (89%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች በህጉ መሰረት የተሰጠውን የአንድ ሰዓት (1፡00 ሰዓት) የምሳ ዕረፍት የተጠቀሙ ሲሆን 200 (11%) ጣቢያዎች ላይ ከአንድ ሰዓት በላይ የምሳ ዕረፍት እንደተጠቀሙ ኅብረቱ ታዝቧል። የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎችን በተመለከተ በ205 (93%) ትዝብት የተደረገባቸው ጣቢያዎች በህጉ መሰረት የተሰጠውን የአንድ ሰዓት የምሳ ዕረፍት የተጠቀሙ ሲሆን 15 (7%) ጣቢያዎች ላይ ከአንድ ሰዓት በላይ የምሳ ዕረፍት መጠቀማቸው ታውቋል።
  • የምዝገባ ጣቢያዎች መዝጊያ ሰዓትን በተመለከተ በከሰዓቱ ክፍለ ጊዜ ትዝብት ከተደረገባቸው 1,902 የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 220 የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች መካከል በ1,686 (89%) የማንዋል እና 193 (88%) የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ከ11፡30 ሰዓት እስከ 12፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ መዘጋታቸው ታውቋል። 137 (7%) የማኑዋል እና 17 (8%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በኋላ መዘጋታቸውን ግኝታችን ያሳያል። በአንጻሩ በ79 (4%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና በ10 (5%) የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ከ11፡30 በፊት መዘጋታቸውን የትዝብት ሪፖርቱ ያሳያል። 
  • የምዝገባ ሂደት መቋረጥን በተመለከተ ኅብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች 2,666 (67%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 320 (72%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የምዝገባው ሂደት በማናቸውም ግዜ አልተቋረጠም። በተቃራኒው በ1,287 (33%) የማኑዋል የምዝገባ ጣቢያዎች እና በ123 (28%) የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ምዝገባ ቢያንስ አንድ ግዜ ተቋርጧል።
  • በምዝገባ ጣቢያዎች የጸሃይ እና የዝናብ መከለያ መኖርን በተመለከተ ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,324 (59%) የማንዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 268 (60%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ተመዝጋቢዎችን ከፀሐይ/ከዝናብ የሚከላከል መጠለያ (ጥላ) ማዘጋጀታቸውን፤ በተቃራኒው 1,629 (41%) በማኑዋል ምዝገባ እና 175 (40%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ግን ከጸሃይ እና ከዝናብ የሚከላከል መጠለያ አልተዘጋጀላቸውም።
  • የምዝገባ ጣቢያዎች አደረጃጀት ለሴት ተመዝጋቢዎች ከመኖሪያ ቦታቸው ያለው ርቀት እና ከደህንነት ስጋት አኳያ ያላቸውን አመቺነት በተመለከተ ኅብረቱ በታዘባቸው 3,563 (90%) የማኑዋል የምዝገባ ጣቢያዎች እና 400 (90%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ለሴቶች አመቺ እንደነበሩ በአንጻሩ ደግሞ 390 (10%) እና 43 (10%) የማንዋል እና የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች እንደቅደም ተከተላቸው ለሴቶች አመቺ አልነበሩም።
  • የምዝገባ ጣቢያዎች የመንቀሳቀስ ውስንነት ላለባቸው ተመዝጋቢዎች (አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች ወይም ጨቅላ ሕጻናትን የያዙ ወላጆች) የነበራቸውን ተደራሽነት በተመለከተ ኅብረቱ ከታዘባቸው 437 (11%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 88 (20%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የመንቀሳቀስ ውስንነት ላለባቸው ተመዝጋቢዎች (አረጋውያን፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች ወይም ጨቅላ ሕጻናትን የያዙ ወላጆች) ተደራሽ እንደነበሩ ሲያመለክቱ በተቃራኒው 3,516 (89%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 355 (80%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ለነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ተደራሽ አልነበሩም።
  • የምዝገባ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን አመቺነት በተመለከተ ኅብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች 485 (12%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 103 (23%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞች ያለ እርዳታ ሊገቡባቸው የሚችሉ እንደነበሩ ሆኖም በ3,468 (88%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና በ340 (77%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የአካል ጉዳተኞች ያለእርዳታ ሊገቡ የማያስችሉ እንደነበሩ ኅብረቱ ታዝቧል። 
  • የኅብረቱ ታዛቢዎች ወደ ምዝገባ ጣቢያዎች ገብተው መታዘብን በተመለከተ በ3,927 (99%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና በ430 (97%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የኅብረቱ ታዛቢዎች ያለ ምንም ክልከላ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል። ሆኖም በ26 (1%) የማኑዋል ምዝገባ እና በ13 (3%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የኅብረቱ ታዛቢዎች ወደ ምዝገባ ጣቢያዎች እንዳይገቡ ተከልክለዋል። 
  • የጸጥታ አስከባሪዎች ኅብረቱ በታዘባቸው 2,999 (76%) የማኑዋል እና በ320 (80%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ከምዝገባ ጣቢያዎች ውጭ መገኘታቸውን ታዝበናል። ከእነዚህ ውስጥ 2003 (51%) የማንዋል እና 219 (49%) የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ላይ የመደበኛ ፖሊስ አባላት ከምዝገባ ጣቢያዎች ውጭ ተገኝተዋል። በተቀሩት 972 (24%) የማንዋል እና 142 (32%) የታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ደግሞ ከመደበኛ ፖሊስ ውጭ ያሉ ሌሎች የፀጥታ አካላት ከምዝገባ ጣቢያዎች ውጭ ተገኝተዋል። 978 (25%) በማንዋል እና 82 (19%) በታብሌት የምዝገባ ጣቢያዎች ደግሞ ፖሊስም ሆነ ሌሎች የፀጥታ አካላት ከምርጫ ጣቢያ ውጪ አልነበሩም።   
  • በምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ እና አካባቢ በተመዝጋቢዎች፣ አስፈጻሚዎች፣ታዛቢዎች ላይ የደረሰ ጥቃት፣ ማስፈራራት፣ ወከባ እና ወዘተ በተመለከተ በ3,942 (99.7%) የማኑዋል እና 438 (99%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ ወይም አካባቢ ከላይ የተዘረዘሩ ድርጊቶች ያልተከሰቱ ሲሆን በ11 (0.03%) የማኑዋል እና በ5 (1%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ ወይም አካባቢ በምርጫ አስፈጻሚዎች ላይ አንድ (1) የግድያ (በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን) ፤ ሁለት (2) የግድያ ሙከራ (አማራ ክልል አዊ ዞን እና ዋግ ህምራ ዞን) ፣ ሰባት (7) አፈና/ዕገታ (በአማራ ክልል በምስራቅ ጎጃም ዞን ሁለት (2) ፤ በዋግ ሕምራ ዞን ሁለት (2) እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ሁለት (2)፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን አንድ (1)) አንድ (1) ድብደባ (ሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን)፣ ስድስት(6) የማስፈራራት (በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን፣ ሰሜን ወሎ ዞን ፤ በምዕራብ ጎጃም ዞን፣ ደቡብ ጎንደር ዞን፣ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን) ተፈጽመዋል። 

የመራጮች ምዝገባ ሂደት

  • በሕጉ መሠረት ማንኛውም ተመዝጋቢ የቀበሌ መታወቂያ ወይም ፓስፖርት (ጊዜው ያለፈበት ቢሆንም)፣ የመንጃ ፈቃድ፣ ከውትድርና የተገለሉበት ማስረጃ፣ የተማሪ መታወቂያ እና የመሳሰሉ ሰነዶችን ለመመዝገብ በማስረጃነት ማቅረብ ይኖርበታል። ትዝብት ከተደረገባቸው በማኑዋል ምዝገባ ካከናወኑ 3,953 የምዝገባ ጣቢያዎች መካከል 3,451 (87%) በህጉ መሰረት ማንነታቸውን እና ነዋሪነታቸውን የሚያረጋግጥ ሰነድ በማቅረብ ተመዝግበዋል። ሆኖም ቁጥራቸው ከአንድ እስከ ሃያ (1 – 20) የሚደርሱ ተመዝጋቢዎች በ494 (12.49%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች ከላይ የተዘረዘሩ ሰነዶችን ሳያቀርቡ ተመዝግበዋል። በተጨማሪም በ8 (0.002%) ጣቢያዎች ከ20 በላይ ተመዝጋቢዎች ማንነታቸውን እና ነዋሪነታቸውን ሳያረጋግጡ ተመዝግበዋል።  
  • በታብሌት ምዝገባ በተደረገባቸው ጣቢያዎች የፋይዳ ብሔራዊ መታወቂያ ላላቸው ተመዝጋቢዎች የአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል (OTP) በተመዘገቡበት ስልክ ቁጥር መላክ ያለበት ሲሆን ፋይዳ ለሌላቸው ተመዝጋቢዎች የምርጫ አስፈጻሚዎች ታብሌቱን በመጠቀም የተመዝጋቢዎችን መረጃ በማስገባት ይመዘግባሉ። በዚህም መሰረት ኅብረቱ ከታዘባቸው 443 የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች መካከል 424 (96%) ወደ ተመዝጋቢው ስልክ የአንድ ጊዜ የይለፍ ቃል ያለምንም መስተጓጎል የኅብረቱ ታዛቢዎች በነበሩበት ሰዓት ሲልክ የነበረ ሲሆን 13 (3%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ቁጥራቸው ከአንድ እስከ ሃያ (1 – 20) ለሚሆኑ ተመዝጋቢዎች የይለፍ ቃል አለመላኩን መታዘብ ተችሏል። በተጨማሪም በ6(1%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ከ20 በላይ ለሚሆኑ ተመዝጋቢዎች የይለፍ ቃል ወደስልካቸው አልተላከም። 
  • የብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ) የሌላቸው የታብሌት ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ በ412 (93%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች መተግበሪያው ተመዝጋቢዎች ያቀረቡትን መረጃ (ስም፣ ዕድሜ፣ ፎቶ እና የመሳሰሉትን) የኅብረቱ ታዛቢዎች በጣቢያው በነበሩበት ሰዓት ሙሉ ለሙሉ አስፈጻሚዎች ወደመተግበሪያው ማስገባታቸውን እና ተቀባይነት ማግኘቱን ታዝበዋል። በተጨማሪም በ26 (6%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ከአንድ እስከ ሃያ (1 – 20) የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች መረጃዎችን አስፈጻሚዎች ወደ መተግበሪያው ማስገባት አለመቻላቸውን እንዲኢሁም በ5 (1%) የምዝገባ ጣቢያዎች ደግሞ ከ20 በላይ ለሆኑ ተመዝጋቢዎች የቀረቡትን ማስረጃዎች ሲስተሙ እንዳልተቀበለ ለመታዘብ ተችሏል። 
  • በማኑዋል የምዝገባ ሂደት መራጮች ምዝገባቸውን እንዳጠናቀቁ ወዲያውኑ የምዝገባ ካርድ ማግኘት እንዳለባቸው የምርጫ ህጉ ይደነግጋል። ኅብረቱ በታዘበባቸው በ3,831 (97%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች ተመዝጋቢዎች እንደተመዘገቡ ወዲያውኑ የመመዝገቢያ ካርዳቸው የተሰጣቸው ሲሆን በ111 (3%) ከአንድ እስከ ሃያ (1 – 20) ተመዝጋቢዎች የምዝገባ ካርድ ወዲያውኑ አልተሰጣቸውም። በተጨማሪም በ11 (0.2%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች ከ20 በላይ ተመዝጋቢዎች የምዝገባ ካርድ ወዲያውኑ አልተሰጣቸውም። 
  • በምርጫ ሕጉ በምዝገባ ጣቢያዎች እንዲገኙ ከተፈቀደላቸው አካላት ማለትም ተመዝጋቢዎች ተመዝግበው እስኪጨርሱ፣ ከምርጫ ቦርድ አስፈጻሚዎችና ሠራተኞች፣ ከፓርቲ ወኪሎች እንዲሁም ዕውቅና ካላቸው ታዛቢዎች ውጭ ማንኛውም ሌላ አካል በጣቢያው ውስጥ መገኘት የተከለከለ ነው። ኅብረቱ ከታዘባቸው ጣቢዎች ውስጥ በ3,870 (98%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና 424 (96%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ያልተፈቀደላቸው ሰዎች በምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ አልተገኙም። ሆኖም ግን በ83 (2%) የማኑዋል እና 19 (4%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ ያልተፈቀደላቸው አካላት (የቀበሌ አመራሮች እና አስተዳደሮች፤ የጸጥታ አካላት፤ የአካባቢ የፓርቲ አስተባባሪዎች) በጣብያዎች ውስጥ ተገኝተዋል። 
  • በምርጫ ሕጉ መሠረት ማንኛውም ተመዝጋቢ በምዝገባ ጣቢያው በአካል ቀርቦ መመዝገብ ያለበት ሲሆን፣ በአካል ሳይቀርቡ መመዝገብ የተከለከለ እንደሆነ ተደንግጓል። ኅብረቱ ከታዘባቸው ጣቢያዎች መካከል በ3,861 (98%) የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች እና በ431 (97%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ተመዝጋቢዎች በአካል ተገኝተው ሲመዘገቡ በ92 (2%) የማኑዋል እና 12 (3%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢዎች ተመዝጋቢዎች በአካል ሳይቀርቡ ተመዝግበዋል። 

አካታችነት 

  • የምዝገባ ጣቢያ አስፈጻሚዎች እና ኃላፊዎች የጾታ እና የአካል ጉዳት ስብጥርን በተመለከተ የኅብረቱ ታዛቢዎች በታዘቧቸው በሁለቱም የምዝገባ አማራጮች ምዝገባ በተደረገባቸው ጣቢያዎች በአማካይ ከተገኙ 4 አስፈፃሚዎች መካካል አንድ ሴት አስፈጻሚ ነበረች። ሴት አስፈጻሚዎች ከተሰማሩባቸው የማኑዋል ምዝገባ ጣቢያዎች መካከል በ672 (17%) ጣቢያዎች ኃላፊዋ ሴት ስትሆን የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎችን በተመለከተ በ109 (25%) ጣቢያዎች ኃላፊዋ ሴት ነበረች። 
  • አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ትዝብት ከተደረገባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች በ93 (0.02%) የማኑዋል እና 15 (0.03%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞች በአስፈጻሚነት የተሳተፉ ሲሆን በእነዚህ ጣቢያዎች አካል ጉዳት ያለባቸው የምርጫ አስፈጻሚዎች በጣቢያ ኃላፊነት ሰርተዋል።
  • ሴት የሰልፍ ተቆጣጣሪዎችን በተመለከተ ኅብረቱ ከታዘባቸው 3,839 (97%) የማኑዋል እና 434 (98%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ሴት የሰልፍ ተቆጣጣሪዎች (ፈታሾች) የነበሩ ሲሆን በ114 (4%) የማኑዋል እና 9 (2%) የታብሌት ጣቢያዎች ላይ ሴት የሰልፍ ተቆጣጣሪዎች (ፈታሾች) አልተመደቡም።
  • በድጋፍ ለሚመዘገቡ ሰዎች የሰጡትን መረጃ ተመዝጋቢው እና ታዛቢዎች መስማት በሚችሉት ልክ ጮክ ብሎ መነበብ እንዳለበት ህጉ ያስቀምጣል። በዚህም መሰረት ኅብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች በ808 (46%) የማኑዋል እና 162 (37%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የተተገበረ ሲሆን፣ በ2,145 (54%) የማኑዋል እና 281 (63%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ግን ይህ አሰራር አልተተገበረም።

የምርጫ ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ 

  • ፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባው ሂደት ግልጽነት እንዲኖረው ለማረጋገጥ እንዲሁም የፓርቲያቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ፣ በምርጫ ቦርድ ዕውቅና ያገኙ ወኪሎቻቸውን በምዝገባ ጣቢያዎች ማሰማራት ይጠበቅባቸዋል። ኅብረቱ ከታዘባቸው የምዝገባ ጣቢያዎች በ539 (14%) የማኑዋል እና በ61 (14%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የፓርቲ ወኪሎች የተገኙ ሲሆን በ3,414 (86%) የማኑዋል እና በ382 (86%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች የፓርቲ ወኪሎች አልተገኙም። 
  • የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የምዝገባው ሂደት አካታች፣ግልጽ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት መሆኑን ለመታዘብ እና ግኝቶቻቸውን ለህዝብ፣ ለምርጫ ቦርድ ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለሚዲያ ለማቅረብ ታዛቢዎችን ያሰማራሉ። ከዚህ አንጻር ኅብረቱ ከታዘበባቸው የማኑዋል እና የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ውስጥ (ከኅብረቱ ታዛቢዎች ውጪ) በ156 (8%) የማኑዋል እና በ52 (12%) የታብሌት ምዝገባ ጣቢያዎች ታዛቢዎች የተገኙ ሲሆን፣ በ1,746 (92%) በማኑዋል ምዝገባ እና በ391 (88%) የታብሌት ጣቢያዎች ታዛቢዎች አልተገኙም። 

በመራጮች ምዝገባ ሂደት የታዩ ጠንካራ ጎኖች፣ መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች እና ምክረ-ሃሳቦች

የታዩ ጠንካራ ጎኖች 

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ የታዩ ጠንካራ ጎኖች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

  • ቦርዱ የመራጮች ምዝገባን በዲጂታል መንገድ ለማከናወን የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ ማዘጋጀቱ፣ ቴክኖሎጂውን ማስተዋወቁ ፣ የአሠራር ስርዓት መዘርጋቱ እና ተግባራዊ ለማድረግ መሞከሩ፤
  • ከ5.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በዲጂታል አማራጭ መመዝገባቸው፤
  • በአጠቃላይ ከ50.5 ሚሊዮን በላይ መራጮች መመዝገባቸውና ከእነዚህም ውስጥ 46% ሴቶች መሆናቸው 
  • አብዛኞቹ የምዝገባ ጣቢያዎች በሕግ በተፈቀዱ ስፍራዎች መቋቋማቸው፤
  • በምዝገባ ጣቢያዎች በአማካይ 4 አስፈፃሚዎች መገኘታቸው፤
  • በ87% ትዝብት በተደረገባቸው ጣቢያዎች መራጮች ማንነታቸውን በሚያረጋግጥ ሰነድ በማቅረብ መመዝገባቸው፤ 
  • ከ97% በላይ በሆኑ ትዝብት የተደረገባቸው ጣቢያዎች የኅብረቱ ታዛቢዎች ያለ ምንም ክልከላ ወደ ምዝገባ ጣቢያ መግባት መቻላቸው፤

ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች

በመራጮች ምዝገባ ላይ የተስተዋሉ እና መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች ከዚህ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡-

  • የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት በተደጋጋሚ መቆራረጡ፤
  • ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ጣቢያዎች በሕግ በተከለከሉ ቦታዎች መቋቋማቸው፤
  • በአንዳንድ የምዝገባ ጣቢያዎች ማንነትን ሳያረጋግጡ መመዝገብ፣ በአካል ያልቀረቡ ሰዎችን መመዝገብ እና በምዝገባ ጣቢያዎች ያልተፈቀደላቸው አካላት መገኘት መስተዋሉ፤
  • ብዙ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞችና ልዩ የመንቀሳቀስ ውስንነት ላለባቸው ዜጎች ተደራሽ አለመሆናቸው፤
  • በታጠቁ ኃይሎች አስፈጻሚዎችና መራጮች ላይ የደረሱ ግድያ፣ ማስፈራራት፣እና የአፈና ድርጊቶች መኖራቸው 

ምክረ-ሃሳቦች

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (ቦርዱ)

  • የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓቱን መሠረተ-ልማት በአስቸኳይ በማጠናከር የሲስተም መቆራረጥ እንዲፈታ ማሻሻያ ማድረግ። 
  • ማንነትን ሳያረጋግጡ መመዝገብ፣ ሰዎችን በአካል ያልቀረቡ ሰዎችን መመዝገብ፤ በምዝገባ ጣቢያዎች ያልተፈቀደላቸው አካላት መገኘት፣ የሕግ ጥሰት መሆኑን አጽንኦት ሰጥቶ በማስገንዘብ፣ ሕጉን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ አግባብነት ያለው እርምጃ መውሰድ።
  • የምዝገባ ጣቢያዎች በሕግ በተፈቀዱ ቦታዎች ብቻ መቋቋማቸውን ጥብቅ ክትትል ማድረግ እና ማረጋገጥ።
  • ለድምፅ መስጫ ቀን የሚደራጁ ምርጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞችና የመንቀሳቀስ ውስንነት ላለባቸው መራጮች አመቺ መሆናቸውን ቢያረጋግጥ። በተጨማሪም፣ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መራጮች ሲመዘገቡ በዕገዛ ያስመዘገቡትን መረጃ ለመራጩ በሚሰማ መልኩ የማንበብ ሕጋዊ አሠራር በሁሉም ጣቢያዎች መተግበሩን በጥብቅ መከታተል።
  • የምርጫ አስፈጻሚዎች በተመደቡበት ጣቢያ አለመገኘት እና የሰዓት አከባበር ችግሮችን ለማሻሻል ጠንካራ ያልተቋረጠ ክትትል ማድግና እና ሥልጠና መስጠት። 
  • የምርጫ ጣቢያዎች ላይ መራጮችን ከፀሐይና ከዝናብ የሚከልል መጠለያ መሰራ ቢያረጋግጥ።

ለክልል መንግስታት

  • የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ የተፈቀዱ ቦታዎች ላይ መቋቋማቸውን፣ ለአካል ጉዳተኞች አመቺ መሆናቸውን እንዲሁም ህጉ በሚያስቀምጠው መሰረት መራጮችን ከጸሃይ እና ከዝናብ የሚከላከል መጠለያ ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል።  

ለጸጥታ አካላት

  • በምርጫ አስፈጻሚዎች፣ መራጮች፣እና ታዛቢዎች ላይ ማስፈራሪያዎች እና ጥቃቶች እንዳይደርሱ ተገቢው ጥበቃ ቢደረግ።
  • በምርጫ ጣቢያዎች ላይ መደበኛ የፖሊሲ አባላትን ከምርጫ ጣቢያው ውጪ በመመደብ ጥበቃ ቢደረግ።

ለፖለቲካ ፓርቲዎች እና ለሲቪል ማህበራት

  • በድምጽ መስጫ ቀን የፓርቲ ወኪሎችን እና ታዛቢዎችን በማሰማራት የምርጫ ሂደቱ ግልጽነት፣ አካታችነት እና ተጠያቂነት እንዲኖረው የማረጋገጥ ሃላፊነታቸውን ቢወጡ።