አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ 

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ)፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአገር በቀል የዜጎች ምርጫ ትዝብት (Citizen Election Observation) ለማከናወን፤ 2,258 ተቀማጭ (Sitting Observers) እና 891 ተንቀሳቃሽ (Mobile Observers) ታዛቢዎችን፣ በአጠቃላይ 3,149 ታዛቢዎችን አሰማርቷል።

የኅብረቱ ተቀማጭ ታዛቢዎች በተመደቡባቸው የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 11፡30 ጀምሮ የጣቢያዎቹን አደረጃጀትና አከፋፈት፣ የድምፅ አሰጣጥና የቆጠራ ሂደቱን፣ እንዲሁም በጣቢያ ደረጃ የሚከናወነውን ይፋዊ የውጤት መለጠፍ ተግባር ይታዘባሉ። በሌላ በኩል፣ እያንዳንዱ ተንቀሳቃሽ ታዛቢ ቢያንስ ስድስት (6) የተለያዩ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን በመዘዋወር እንዲታዘብ ተመድቧል።

የኅብረቱ ታዛቢዎች ስምሪት፤ ከትግራይ ክልል፣ በአማራ ክልል ከሚገኙ ስምንት (8) የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም አከራካሪ ከሆኑ 5 የምርጫ ክልሎች ውጭ ባሉ የምርጫ ክልሎችን የተከናወነ ነው። ይህ የስምሪት ስልት በየክልሎቹ ያለውን የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት መሠረት ባደረገ ተመጣጣኝ (proportional) ትዝብት ዘዴ ላይ የተመሠረተ ነው። 

ይህ የእኩለ ቀን የትዝብት ሪፖርት መሰረት ያደረገው የኅብረቱ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው 2,258 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ ነው። ኅብረቱ ካሰማራቸው ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች የሰበሰባቸው መረጃዎች አሳሳቢ ሁነቶች ላይ የተደረጉ ሪፖርቶች ብቻ ነው። የኅብረት ለምርጫ የመረጃ ማዕከል በድምጽ መስጫ ቀን እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ ከተቀበላቸው 2,258 ተቀማጭ ታዛቢዎች (Stationary Observers) ባቀረቧቸው ሪፖርቶች ላይ ተመስርቶ ተዘጋጅቷል። 

በሚጠበቁ ነገር ግን በዘገዩ መረጃዎች ምክንያት ይህ ሪፖርት ያላካተታቸው የትዝብት ግኝቶች ያሉ ሲሆን ዘግይተው የሚደርሱ መረጃዎች ኅብረቱ በሚያወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ውስጥ ተካተው የሚቀርቡ ይሆናል። ይህ የእኩለ ቀን ሪፖርት የኅብረቱ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው 2,258 ጣቢያዎች አስር (10) ዋና አመላካቾች (Indicators) ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው። 

ዋና ዋና የእኩለ ቀን ትዝብት ግኝቶች

  1. ታዛቢዎች ወደ ድምጽ መስጫ ጣቢያ በመግባት እንዲታዘቡ መፈቀድ

የምርጫ ህጉ ከቦርዱ እውቅና የተሰጣቸው የምርጫ ታዛቢዎች በተመደቡበት የድምፅ መስጫ ጣቢያ ገብተው ሂደቱን በነፃነት መታዘብ እንደሚችሉ ይደነግጋል። የኅብረቱ ታዛቢዎች ወደ ምርጫ ጣቢያ ገብተው እንዲታዘቡ መፈቀድን በተመለከተ፣ ከተቀብልናቸው ሪፖርቶች መካከል 2,241 (99%) የሚሆኑት ያለምንም ገደብ ወደ ጣቢያዎቹ ገብተው መታዘብ ችለዋል።

በተቃራኒው ግን 17 (1%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን ታውቋል።

  1. በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች መክፈቻ ሰዓት የምርጫ አስፈጻሚዎች ተሟልቶ መገኘት

የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ በተደነገገው የመክፈቻ ሰዓት ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ከመከፈታቸው በፊት የምርጫ አስፈፃሚዎች በቦታው መገኘት ይጠበቅባቸዋል። ይህ የምርጫ ጣቢያው በወቅቱ እንዲዘጋጅ፣ የምርጫ ቁሳቁሶች እንዲደርሱ እና የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ በሥርዓት እንዲጀመር ቅድመ ሁኔታ ነው። ኅብረቱ ከተቀበላቸው የትዝብት ረፖርቶች ውስጥ 2,183 (97%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች፣ የኅብረቱ ታዛቢዎች በምርጫ ጣቢያ ሲደርሱ የምርጫ አስፈጻሚዎች በቦታው እንደነበሩ ታዝበናል።

በተቃራኒው፣ 50 (2%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች፣ የኅብረቱ ታዛቢዎች ሲደርሱ የምርጫ አስፈጻሚዎች ከመክፈቻው ሰዓት (ንጋት 12 ሰዓት) በቦታው እንዳልተገኙ ታዝበናል። 

  1. ድምጽ መስጠት በሚጀመርበት ሰዓት (ከጠዋቱ 12 ሰዓት) በጣቢያዎች የተገኙ አስፈጻሚዎች ቁጥር

የድምፅ አሰጣጥ በሚጀምርበት ወቅት በ2,146 (95%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ከ3 በላይ የምርጫ አስፈጻሚዎች በህጉ በተደነገገው መሰረት በቦታው ተገኝተው ሥራ መጀመራቸውን ኅብረቱ ታዝቧል። በአንጻሩ 90 (4%) ጣቢያዎች ውስጥ ደግሞ 3 የምርጫ አስፈጻሚዎች በምርጫ ጣቢያዎች መገኘታቸው ሲረጋገጥ፣ በተቃራኒው በ22 (1%) የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ውስጥ ከ3 በታች የምርጫ አስፈጻሚዎች መገኘታቸውን መታዘብ ተችሏል።

  1. የምርጫ አስፈፃሚዎች የፆታ እና የአካል ጉዳተኝነት ስብጥር

ከታዘብናቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መካከል በ1,380 (61%) ጣቢያዎች ከ1 በላይ ሴት የምርጫ አስፈጻሚዎች ሲገኙ፤ በአንጻሩ 697 (31%) ድምጽ መስጫ ጣቢያ 1 ሴት አስፈጻሚ እንደነበረች ታዝበናል። በተቃራኒው በ181 (8%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ውስጥ ደግሞ ምንም ዓይነት ሴት የምርጫ አስፈጻሚዎች እንዳልተመደቡ ታዝበናል።

ትዝብት ከተደረገባቸው የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መካከል 76 (3%) በሚሆኑት ከ1 በላይ አካል ጉዳተኛ የምርጫ አስፈጻሚዎች ተገኝተዋል። በሌላ በኩል 224 (10%) ጣቢያዎች ውስጥ 1 አካል ጉዳተኛ አስፈጻሚ መገኘታቸውን ታዝበናል። በአንጻሩ በ1,958 (87%) ጣቢያዎች ደግሞ ምንም ዓይነት አካል ጉዳተኛ የምርጫ አስፈጻሚ እንዳልነበረ መታዘብ ተችሏል።

የምርጫ ጣቢያ ኃላፊዎች የጾታ ስብጥርን በሚመለከት፣ በ587 (26%) ጣቢያዎች ውስጥ የድምጽ መስጫ ጣቢያው ኃላፊ ሴት ነበረች። በተመሳሳይ ሁኔታ በ54 (2%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች አካል ጉዳተኛ ሴቶች በጣቢያ ኃላፊነት መስራታቸውን፣ በ65 (3%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ደግሞ አካል ጉዳተኛ ወንዶች የጣቢያ ኃላፊ ሆነው መስራታቸውን ታዝበናል።

  1. የድምፅ መስጠት አጀማመር

ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,258 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መካከል፣ በ947 (42%) ጣቢያዎች የድምፅ መስጠት ሂደቱ ከጥዋቱ 12 ሰዓት በፊት መጀመሩን፣ በ1,276 (57%) ጣቢያዎች ደግሞ ከጥዋቱ 12 እስከ 1 ሰዓት ባለው ግዜ መጀመሩን ኅብረቱ ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 32 (1%) ጣቢያዎች የድምፅ አሰጣጥ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት በኋላ መጀመሩን ኅብረቱ የታዘበ ሲሆን በ3 ጣቢያዎች ይህ መግለጫ እስከተዘጋጀበት ሰዓት ድረስ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት እንዳልተጀመረ ለመታዘብ ተችሏል።

  1. የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ሥፍራ

በምርጫ ህጉ መሰረት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በወታደራዊ ካምፕ፣ ፖሊስ ጣቢያ፣ የሃይማኖት ተቋም፣ የጤና ተቋም፣ መጠጥ ቤት/ሆቴል፣ የፖለቲካ ፓርቲ ጽ/ቤት ወይም የግለሰብ መኖሪያ ቤት ማቋቋም የተከለከለ ነው። 

ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,258 ጣቢያዎች መካከል፣ 2,182 (97%) ጣቢያዎች በሕግ በተፈቀዱ ቦታዎች መቋቋማቸውን ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 76 (3%) ጣቢያዎች በሕግ በተከለከሉ ቦታዎች መቋቋማቸውን ታዝቧል።

  1. በድምጽ መስጫ ጣቢያ ውስጥ ወይም በ200 ሜትር ርቀት ክልል ውስጥ የቅስቀሳ ምልክቶች እና ቅስቀሳዎች መኖራቸውን በተመለከተ

ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,258 ጣቢያዎች መካከል፣ 2,171 (96%) ጣቢያዎች በምርጫ ጣቢያው ውስጥ ወይም በ200 ሜትር ርቀት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ ምልክቶች (ፖስተር) ወይም ቅስቀሳዎች አለመከናወናቸውን ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 87 (4%) ጣቢያዎች ውስጥ ወይም በ200 ሜትር ርቀት ክልል ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲ ቅስቀሳ ምልክቶች፣ ቁሳቁሶች ወይም የቅስቀሳ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን ታዝበናል።

  1. የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ተደራሽነት እና አመቺነት በተመለከተ

በምርጫ ህጉ መሰረት የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች በሕግ በተፈቀዱ ቦታዎች መቋቋም፣ ለመራጮች በቀላሉ ተደራሽ መሆን እና መሠረታዊ የምርጫ ቁሳቁሶች ተሟልተው መገኘታቸው የድምፅ አሰጣጥ ሂደት በሥርዓት እንዲካሄድ አስፈላጊ ነው። በተለይ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ለአረጋውያን፣ ለነፍሰ ጡሮች እና ጨቅላ ሕፃን ለያዙ ወላጆች ተደራሽነት መኖሩ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።

የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች የተቋቋሙበት ስፍራ ለሴቶች ያላቸውን አመቺነትን በተመለከተ ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,258 ጣቢያዎች መካከል፣ 2,157 (96%) ጣቢያዎች ለሴቶች ምቹ እንደነበሩ ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 101 (4%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ለሴቶች አመቺ እንዳልነበሩ መታዘብ ተችሏል።

የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ያላቸውን ተደራሽነት በተመለከተ፣ ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,258 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መካከል፣ 2,110 (93%) ጣቢያዎች አካል ጉዳተኞች ያለ ረዳት በመግባት ድምፅ ለመስጠት ምቹ እንደነበሩ ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 148 (7%) ጣቢያዎች ለአካል ጉዳተኞች ምቹ እንዳልነበሩ ታዝበናል።

ጣቢያዎች ለአረጋውያን፣ ለነፍሰ ጡሮች፣ ጨቅላ ሕፃን ለያዙ ወላጆች እና የመንቀሳቀስ ችግር ላለባቸው መራጮች ያላቸውን አመቺነት በተመለከተ 2,158 (96%) ጣቢያዎች ምቹ እንደነበሩ ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 100 (4%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች በዚህ ረገድ ችግር እንደነበረባቸው ለመታዘብ ተችሏል።

  1. ሁሉም የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች መሟላታቸውን በተመለከተ

ኅብረቱ ትዝብት መሠረት፣ የድምፅ መስጫ ወረቀቶች፣ የቦርዱ ማህተም፣ የማይለቅ የጣት ቀለም፣ የድምፅ መስጫ ማሸጊያዎች፣ የመራጮች መዝገብ እና የቦርዱ ድምፅ መስጫ ሳጥኖች ጨምሮ የምርጫ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ በታዘቡት ጣቢያዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል። በተቃራኒው፣ የውጤት መግለጫ እና ማመሳከሪያ ፎርም 99% (1,693) ሲገኝ በ1% (11) ጣቢያዎች ላይ አልተገኘም፤ እንዲሁም የቅሬታ ማቅረቢያ እና ምስክርነት መቀበያ ፎርም 99% (1,680) ሲገኝ በ1% (24) ጣቢያዎች ላይ አለመገኘቱ ተመዝግቧል። 

  1. የድምፅ መስጫ ሳጥኖች ከመታሸጋቸው በፊት ባዶ መሆናቸውን ማረጋገጥን በተመለከተ

ኅብረቱ ከታዘባቸው 2,258 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች መካከል፣ 2,232 (99%) ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ሳጥኑ ከመታሸጉ በፊት ባዶ መሆኑ ታዝቧል። በተቃራኒው፣ 26 (1%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች የድምፅ መስጫ ሳጥኑ ከመታሸጉ በፊት ባዶ መሆኑ በግልፅ እንዳልታየ መታዘብ ተችሏል። በ2,253 ጣቢያዎች የድምጽ መስጫ ማሸጊያዎች መገኘታቸው የታዘብን ሲሆን በ5 ጣቢያዎች ደግሞ የድምጽ መስጫ ማሸጊያዎች አለመገኘታቸውን ታዝበናል።

አሳሳቢ ሁነቶች

ይህ የእኩለ ቀን ሪፖርት በሚዘጋጅበት ጊዜ፣ ኅብረት ለምርጫ ከመክፈቻና ከዝግጅት ሂደት ጋር የተያያዙ  በጠቅላላው 203 አሳሳቢ ሁነቶችን የተቀበለ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 40 ያህሉ የተረጋገጡ ናቸው። ሪፖርቶ የተደረጉ 163 ጉዳዮች ገና በማረጋገጥ ሂደት ላይ የሚገኙ ሲሆን ዝርዝር መረጃዎችን ኅብረቱ በሚያወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ይፋ የሚያደርግ ይሆናል። 

  1. በተከለከለ ቦታ የተቋቋሙ ጣቢያዎች

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያና ገምዛ  ምርጫ ጣቢያ የተቋቋመው ጤና ጣቢያ ውስጥ ሲሆን ስሙም መኮይ ጤና 3 ለ _1 ምርጫ ጣቢያ ይባላል። በአዲስ አበባ የካ ወረዳ 1 የሚገኝ ምርጫ ጣቢያ የተቋቋመው በጤና ጣቢያ ግቢ ውስጥ በተተከል ድንኳን ነው። በድሬደዋ ከተማ አስተደደር ወረዳ 02 የሚገኝ የምርጫ ጣቢያ ሳቢያን አንደኛ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ አንድ ክፍል በመውሰድ ምርጫ እየተደረገ ይገኛል።

  1. በጣቢያዎች ውስጥ ወይም 200 ሜትር ርቀት ላይ ቅስቀሳ ማድረግ

በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ  ወረዳ 4 ምርጫ ጣቢያ ሠፈረ ሰላም ቅድመ አንደኛ ት/ቤት የብልፅግና ፓርቲ ወኪል የቅስቀሳ መልዕክቶችን ሲያስተላልፍ ታዝበናል። በተመሳሳይ በሲዳማ ክልል ሀዋሳ ከተማ አስተዳደር በሚገኝ ምርጫ ጣቢያ 0851207010120 የብልፅግና ፓርቲ ታዛቢ መራጮች ለመምረጥ በተሰለፉበት የምርጫ ቅስቀሳ ሲይያደርግ ታይቷል።

  1. ታዛቢዎች ወደጣቢያ እንዳየግቡ መከልከል  

የኅብረቱ ታዛቢ ወልዲያ ጉዲና ምርጫ ጣቢያ እንዳይገባ የተከለከለ ሲሆን ቀደም ብሎ ምርጫ ጣቢያ ሲደርስ ለምርጫ አስፈጻሚው የመጣበትን ቢናገርም እንዲሁም መታወቂያ ቢያሳይም እንዲገባ አልተፈቀደለትም። 

በኦሮሚያ ክልል ኢሉ አባ ቦራ ዞን አልጌ ሳቺ ወረዳ በጣቢያ መ.ቁ 422111281401 ታዛቢያችን በሰዓቱ በጣቢያው ቢደርሱም በምርጫ አስፈጻሚው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይገቡ ተከልክሏል።

በኦሮሚያ ክልል በኢሉ አባ ቦራ ዞን ኤልጌ ሰቸ ወረዳ በ አልጌ ምርጫ ጣቢያ በምርጫ ጣቢያ ቁጥር 422111281401 ታዛቢው ጠዋት 12፡00 ሰዓት ደርሰው እንዲገቡ ተፈቅዶላቸው ከገቡ በኋላ እዚያው ቁጭ ብለው እንዲታዘቡ ባለመፍቀድ ታዛቢውን አስወጥተዋቸዋል። 

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አዳሜ ምርጫ ጣቢያ ሀ 1 ታዛቢው የቀበሌ መታወቂያ አልያዝኩም ነገር ግን ሙሉ ስም የሚገልጽ ፎቶ ያለው የመስሪያ ቤት መታወቂያ ከኅብረቱ የትዝብት ባጅ ጋር ቢያሳይም የቀበሌ መታወቂያ ካላመጡ እንደማይታዘቡ ተነግሯቸው ወደ ምርጫ ጣቢያ ገብቶ ለመታዘብ ተከልክለዋል።  

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን ዱና ወረዳ ጨፍሜራ ክራይ ቤት ምርጫ ጣቢያ ቁጥር 0748215020104 ታዛቢዋ ባጅ ላይ የሚታዘቡብት ቦታ በባጁ ላይ አልተጠቀሰም በሚል ምክንያት ገብተው መታዘብ ተከልክለዋል፡፡ 

  1. ከምርጫ ጣቢያ ኃላፊ ውጭ የተደረገ ተደጋጋሚ ዕገዛ 

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ምርጫ ጣቢያ ሠፈረ ሰላም ቅድመ አንደኛ ት/ቤት ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች ለመራጮች ተደጋጋሚ ዕገዛ ሲይደርጉ ነበር። 

በአዲስ አበባ በቂርቆስ ከፍለ ከተማ ወረዳ 03 በ እድር ቤት ምርጫ ጣቢያ  አንድ ዕገዛ እንድታደርግ ያልተፈቀደላት ሴት ከ14 በላይ መራጮች ስትረዳ ከቆየች በኋላ የጣቢያው ኃላፊ እንድትወጣ ተደርጋለች። 

በሰሜናዊ ሲዳማ ጎርቼ ወረዳ ዶና ምርጫ ጣቢያ  ልዩ ስሙ ጎርቼ 01  ምርጫ ጣቢያ ቁጥር 0850910042012 ሰልፍ አስከባሪው ለ30 መራጮች እርዳታ ሲሰጡ አረጋግጠናል። በኦሮሚያ ክልል ነቀምቴ ከተማ አስተዳደር ቡርቃ ጃቶ በምርጫ ጣቢያ ቁጥር 0432405390101 የምርጫ አስፈፅሚ እርዳታ ለሚፈልጉትም ለማይፈልጉትም እየገባ ከአንድ ጊዜ በላይ እገዛ ሲሰጥ ታይቷል። በአማራ ክልል አዊ ዞን ዝገም ወረዳ በምርጫ ጣቢያ ቁጥር 0315105111302 ለመራጮቹ ካርድ የሚሰጡት ምርጫ አስፈፃሚዎች ለ10 መራጮች ምልክት እያደረጉ ሲሰጡ መታዘብ ተችሏል።

  1. የድምጽ መስጫ ሳጥኖች ባዶ መሆናቸውን ሳይረጋገጡ ማሸግ 

ኦሮሞያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ሃሩ ወረዳ ገነት አቦ ቀበሌ ገነት አቦ ምርጫ ጣቢያ ኮድ 0426401691801 ታዛቢያችን ባደረጉት ትዝብት የድምፅ መስጫ ሳጥን ባዶ መሆኑን ሳያሳዩ ማስጀመራቸውን ለመታዘብ ችለዋል። 

  1. የድምጽ መስጫ ወረቀቶችን ማህተም ሳያደርጉ ማደል 

አዲስ አበባ ከተማ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7ተስፋ ብርሃን ሸማቾች ምርጫ ጣቢያ ቁጥር 1452706030103 ታዛቢያችን ጠዋት 1፡30 ላይ ባደረጉት ትዝብት 15 የሚሆኑ መራጮች የተሰጣቸው የድምፅ መስጫ ወረቀት ላይ ምንም አይነት ማህተም እንደሌው ለመታዘብ ችለዋል።  

  1. የድምጽ መስጫ ጣቢያ ቁሳቁሶች መቀያየር 

በአዲስ አበባ ከተማ ለሚ ኩራ ክ/ከተማ አያት ዞን 3  ንኡስ ምርጫ ጣቢያ  ምርጫ ክልል 28  የተወዳደሩት እጩዎች ወደ ምርጫ ክልል 17  ተሳስቶ በመላኩ እስኪስተካከል ድረስ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ ድምጽ መቀጠሉን ታዝበናል።

  1. የጸጥታ መደፈርስ 

ከጸጥታ መደፍረስ ጋር በተገናኘ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ወገራ ወረዳ አምባጊዮርጊስ ከተማ ምርጫ ጣቢያ ቁጥር 031750508100 (ቀበሌ 02) ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት ጀምሮ ድምፅ መስጠት ቢጀመርም፣ ከረፋዱ 5፡10 ጀምሮ በጣቢያው አቅራቢያ በተሰማ ተኩስ ምክንያት ሂደቱ ተቋርጧል። 

በተመሳሳይ በሰሜን ወሎ ጋዞ ወረዳ መቄት 2 ምርጫ ጣቢያ ቁጥር 0314019071101 ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ በነበረ ተኩስ ለ40 ደቂቃ ያህል ሂደቱ ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ ወረዳ በሌላ ጣቢያ ደግሞ ከጠዋቱ 12፡30 እስከ 1፡10 ድረስ በተሰማ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ምክንያት የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ተቋርጦ ከጠዋቱ 1፡30 በኋላ ሂደቱ ቀጥሏል። 

በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ (ጣቢያ ቁጥር 0310718140216) በተኩስ ድምጽ ምክንያት ሂደቱ ሲቋረጥ፣ በፎገራ ወረታ ከተማ (ጣቢያ 0311116140402)። 

በደብረ ታቦር ከተማ ቀበሌ 4 ጣቢያዎችም በተመሳሳይ ምክንያት አስፈጻሚዎች ጣቢያዎቹን ዘግተው ለመውጣት ተገደዋል። በደብረ ታቦር ያለው ጣቢያ በ3፡00 ሰዓት ድጋሚ ስራ የጀመረ ሲሆን፣ በእናቲቱ ማርያም ጣቢያ (0310718140107) ደግሞ በ2፡35 በተከፈተ ተኩስ ሰራተኞች ንብረት ጭነው በመውጣታቸው ሂደቱ ተቋርጧል። 

  1. ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች 

በ አማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ለጋምቦ ወረዳ በአቀስታ ምርጫ ጣቢያ አንድ በ ምርጫ ኮድ 013403070301ላይ ያልተፈቀደላቸው የመንግስት አመራሮች ገብተው አይተው ወጥተዋል።

በሲዳማ ክልል ሃዋሳ ከተማ አስተዳደር ቱላ ወረዳ መሳፍንት ዘለቀ ኪራይ ቤት ምርጫ ጣቢያ በምርጫ ኮድ 851206011111 ላይ ያልተፈቀደላቸው የቀበሌው አመራሮች ወደ ሚስጥራዊ ድምጽ መስጫ ቦታ በመሄድ መራጮችን ሲያስገድዱ እንደነበር ታዝበዋል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ለተጨማሪ መረጃ፦
የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ /ኅብረት ለምርጫ /
ኢሜይል: info@cecoe.org | www.cecoe.org