የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የእኩለ ቀን የትዝብት ሪፖርት

የኢትዮጵያ የሲቪል ማኅበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ (ኅብረት ለምርጫ)፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የአገር በቀል የዜጎች ምርጫ ትዝብት (Citizen Election Observation) ለማከናወን፤ 2,258 ተቀማጭ (Sitting Observers) እና 891 ተንቀሳቃሽ (Mobile Observers) ታዛቢዎችን፣ በአጠቃላይ 3,149 ታዛቢዎችን አሰማርቷል።

የኅብረቱ ተቀማጭ ታዛቢዎች በተመደቡባቸው የድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ከንጋቱ 11፡30 ጀምሮ የጣቢያዎቹን አደረጃጀትና አከፋፈት፣ የድምፅ አሰጣጥና የቆጠራ ሂደቱን፣ እንዲሁም በጣቢያ ደረጃ የሚከናወነውን ይፋዊ የውጤት መለጠፍ ተግባር ይታዘባሉ። በሌላ በኩል፣ እያንዳንዱ ተንቀሳቃሽ ታዛቢ ቢያንስ ስድስት (6) የተለያዩ የድምጽ መስጫ ጣቢያዎችን በመዘዋወር እንዲታዘብ ተመድቧል።

የኅብረቱ ታዛቢዎች ስምሪት፤ ከትግራይ ክልል፣ በአማራ ክልል ከሚገኙ ስምንት (8) የምርጫ ክልሎች፣ እንዲሁም አከራካሪ ከሆኑ 5 የምርጫ ክልሎች ውጭ ባሉ የምርጫ ክልሎችን የተከናወነ ነው። ይህ የስምሪት ስልት በየክልሎቹ ያለውን የምርጫ ጣቢያዎች ብዛት መሠረት ባደረገ ተመጣጣኝ (proportional) ትዝብት ዘዴ ላይ የተመሠረተ ነው። 

ይህ የእኩለ ቀን የትዝብት ሪፖርት መሰረት ያደረገው የኅብረቱ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው 2,258 የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ላይ ብቻ ነው። ኅብረቱ ካሰማራቸው ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎች የሰበሰባቸው መረጃዎች አሳሳቢ ሁነቶች ላይ የተደረጉ ሪፖርቶች ብቻ ነው። የኅብረት ለምርጫ የመረጃ ማዕከል በድምጽ መስጫ ቀን እስከ ቀኑ 7 ሰዓት ድረስ ከተቀበላቸው 2,258 ተቀማጭ ታዛቢዎች (Stationary Observers) ባቀረቧቸው ሪፖርቶች ላይ ተመስርቶ ተዘጋጅቷል። 

በሚጠበቁ ነገር ግን በዘገዩ መረጃዎች ምክንያት ይህ ሪፖርት ያላካተታቸው የትዝብት ግኝቶች ያሉ ሲሆን ዘግይተው የሚደርሱ መረጃዎች ኅብረቱ በሚያወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት ውስጥ ተካተው የሚቀርቡ ይሆናል። ይህ የእኩለ ቀን ሪፖርት የኅብረቱ ታዛቢዎች በተሰማሩባቸው 2,258 ጣቢያዎች አስር (10) ዋና አመላካቾች (Indicators) ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው። 

1 file
pdf
የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የእኩለ ቀን የትዝብት ሪፖርት (1).pdf
288.06 KB